fbpx
AMHARIC

ይሄ የዘር ፖለቲካ፣ የብሔር ጥላቻ … ሊነጋ ሲል በጣም ይጨልማል

ይሄ የዘር ፖለቲካ፣ የብሔር ጥላቻ፣ አንዱን አንዱን ላጥፋህ ባይነት የሃያ አምስት ዓመት ውጤት ነው፡፡ በሁለት ወር አይፈታም፡፡

ጥሩ ሐኪም የሆኑት ዶክተር አብይ ፈውሳችንን እውን እስኪያደርጉት ከጎናቸው ልንቆም ይገባል፡፡ ሊነጋ ሲል በጣም ይጨልማል፤ ***** ስናፍቅሽ አዲስ በድሬቲዩብ

በማቴዎስ ወንጌል ያነበብነውን የመጨረሻ ዘመን ምልክት የምናይ እስኪመስለን ድረስ ደስ የማይሉ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡ ግን የትም አይደርሱም፡፡

እርግጥ ነው ምትክ የሌለው የሰው ልጅ በስቆቃ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬም በዘር ዜማ፣ በልዩነት መዝሙር ወገን በወገኑ ላይ እጁን ያነሳል፡፡ ግን እንዲህ ያሉ ክፉ እጆች መሰብሰቢያቸው ወቅት ደርሷል፡፡

ይሄ የዛሬ አበሳ አይደለም፤ ሃያ አምስት አመት የእኔ የአንተ ብለን አይደለም ምድሩን ሰማዩን ተካለንዋል፡፡

በአንድ ሀገር የምንኖር የብዙ ሀገር ህዝቦች ሆነናል፡፡ ወንዜነትና ጎጠኝነት ተንሰራፍቶ የጋራ ጠላታችን በሆኑት ጭቆና፣ ሙስና ድህነት ላይ እንዳንዘምት ሆነናል፡፡ ሲረግጡን ዝም ያልነው ስለተለያየን ነበር፤ የተለያየ ህዝብ ፈሪ ነው፡፡

የተለያየ ህዝብ የአምባገነኖች መጫወቻ ነው፡፡ የተለያየ ህዝብ ዕጣ ፈንታው ስደት ሞትና መከራ ነው፡፡ እንዲህ ሆነን ሳለ ሌላ መልካም ቀን መጣ፡፡ አንመካም፤ በጠቅላያችንም አንመካም፡፡ ቄሮ በወረወረው ድንጋይም አንመካም፤ እንደ ህዝብ ሆ ብለን በመውጣት ድል በማድረግም አንመካም፤ ከዚህ ሁሉ አበሳ እረፉ ሲለን ፈጣሪ መልካሙን አደረገልን፡፡ አሁን ሊነጋ ነው፡፡ ሊነጋ ሲል ይጨልማል የምንል ህዝቦች ከማቅላላቱ በፊት ያለውን ሰዓት ታግሰንና ተጋግዘን ማለፍ ይኖርብናል፡፡

ኢትዮጵያ ከኢሮብ ጫፍ እስከ ጋምቤላ፣ ከቡሬ እስከ መተማ ብርሃን የምታይበት ዘመን የቀረበላት ሀገር ናት ብለን እንተባበር፤ በሽታው ከመዳኑ በፊት ህመሙ ይጠናል፡፡

ዶክተር አብይ ጥሩ ሐኪም ናቸው፡፡ ወደ ፈውስ እየወሰዱን ነው፡፡ ሁሉም የሚድንባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር፣ የሁሉም ሀገር የሆነችውን ባለ ገናና ታሪክ ኢትዮጵያ ትንሳኤ እውን ለማድረግ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል፡፡ ከዶክተሩ ጎን መቆም ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ነው፡፡

ፈጣሪም ቢሆን ሰው ይልካል እንጂ ራሱ በአካል አይወርድም ይሉናል አባቶቻችን፤ በተለያየ አቅጣጫ የሚሰማውን የሚያስፈራ ድምጽ እናልፈዋለን፡፡

ጆሮአችን የኢትዮጵያን መልካም ዜና እንዲሰማ ዛሬ መልካም ሆነን በሀገር ፍቅር ስሜት በአንድነት መነሳት ይኖርብናል፡፡

ልዩነትን እናሸንፈው፣ ዘረኝነት ማቆሚያ የለውም፡፡ ምድራችን ሰፊ ናት ብለን ልባችንን እናስፋ፤ ሩቅ የለም፡፡ ደስ የምትለዋን ሀገር የምናቀርባት እኛ ነን፡፡

እኩል የምንታይባት፣ እኩል የምንኖርባት፣ እኩል የምንደሰትባት ሀገር እንፍጠር፤ እናም ከመሪያችን ጎን ቆመን የጥላቻ ልዩነትን አጋድመን እንረደው፤ ለወገን የመዘዝነውን ቆንጨራ ጥላቻን እንረድበት፣ ለወገን የሳብነውን ካራ ልዩነትን እንበጥስበት፣ እናም አንድ ሀገር ትኑረን፤ አንድ የጋራ ሀገር፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram