ሰበር ዜና – ቅ/ሲኖዶስ ከነገ ሚያዝያ ፲፬ ቀን ጀምሮ የሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ ዐወጀ፤ ቤተሰቦች የተሠው ክርስቲያኖችን ፎቶ፣ ስመ ክርስትና እና ሙሉ አድራሻ እንዲያቀርቡ አዘዘ – ‹‹ልጆቻችን የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን ናቸው››

pat mat

  • ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹ግፉዓን ይትመሰጥዋ ለመንግሥተ ሰማያት፤ በሃይማኖታቸው ምክንያት ግፍ የሚደርስባቸው መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል››(ማቴ.11÷12) በሚል ርእስ በሰሜን አፍሪቃ ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀልን በተመለከተ ዛሬ፣ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀትር ላይ በድጋሚ ባወጣው ባለዘጠኝ ነጥብ ወቅታዊ የአቋም መግለጫ፡- በግፍ የተሠውት ክርስቲያኖች፣ ሃይማኖታችንን አንክድም በማለት የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን መኾናቸውን አረጋገጠ፤ ቤተሰቦቻቸውንም አጽናና፡፡

Qirqos parents and relatives mourns‹‹የመዋች ቤተሰቦች የኾናችሁ ወገኖቻችን ኹሉ፡-
በዚኽ ግፍ የተሞላበት ጭካኔ የገደሉት ልጆቻችን በዚኽ ዓለም የመኖር መብታቸው በአጭሩ ቢቀጭም ጌታችን፣ ‹‹የተገፉ መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል ማለትም ይወርሷታል›› ባለው አምላካዊ ቃለ እግዚአብሔር፣ ዕንባቸውን አብሶ በመንግሥቱ የሚቀበላቸው መኾናቸውን ዐውቃችኹ፤

እንደዚኹም ልጆቻችን ‹‹ወኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት፤ እስከ ሞት ድረስ የታመንኽ ኹን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለኹ፤››(ራእይ 2÷10) ያለውን የጌታችንን ቃል ጠብቀው ሃይማኖታችንን አንክድም በማለት በሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን ስለኾኑ የጀግና እናት አታለቅስም እንደተባለው የልጆቻችኹ ሰማዕትነት በእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅ ዋጋ ስላላቸው በዚኽ ከሐዘናችኹ እንድትጽናኑ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች፡፡››


  • ከነገ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለ7 ቀናት ያኽል በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በግፍ ለተገደሉት ወገኖች ጸሎተ ፍትሐት፤ ለሀገራችን እና በአጠቃላይ ለዓለሙ ኹሉ ሰላም መጠበቅ፣ ለሰው ልጆች በሕይወት የመኖር መብት መከበር ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡

Holy Synod on the excution of Eth Ortho christians in Libyaነገ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 14 ቀን ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ÷ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መላው የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ ካህናት እና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች እንዲኹም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ሓላፊዎች እና ልዩ ልዩ ሠራተኞች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ወንጌል ይከናወናል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ ዛሬ፣ ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ የሊቢያ የሃይማኖት መስተጋድላን ቤተ ሰዎችን እና ወዳጆችን በየአጥቢያው በአካል እየተገኙ የሚያጽናኑበት መርሐ ግብር ይካሔዳል፡፡


  • በየትኛውም አካባቢ የሚገኙትን ወገኖቻችንን እና የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ከመሰል ጥቃት ለመታደግ እንዲቻል ከመንግሥት ጋራ በቅርበት የሚሠራ ዐቢይ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ ይቋቋማል፡፡
  • ነገ ሚያዝያ 14 ቀን ከጠዋቱ 3፡00 – 4፡30 በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የካህናት አስተዳደር መምሪያ አስፈጻሚነት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት የሚከናወነው የጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ወንጌል ሥነ ሥርዐት፣ በደቡብ አፍሪቃ በግፍ የተገደሉ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንንም ይጨምራል፡፡
  • በሃይማኖታቸው ምክንያት ለተሠዉ ክርስቲያኖች ሊሰጥ የሚገባውን የሰማዕትነት ክብር በቀኖናው መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ መፈጸም ይቻል ዘንድ፣ በአይ ኤስ አሸባሪ ቡድን በግፍ የተገደሉት ልጆቻችን ቤተሰብ የኾናችኁ ሁሉ የመዋቾቹን ስመ ክርስትና፣ ፎቶ እና ሙሉ አድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተቻለ መጠን በፍጥነት እንድታቀርቡ ቤተ ክርስቲያን አሳስባለች፡፡
  • የተፈጸመው የግድያ ወንጀል፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይኾን በኹሉም የዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተቃጣ የወንጀል ተግባር መኾኑን በማመን መላው የሀገራችን ሕዝቦች እና የሃይማኖት ተቋማት እንደዚኹም የዓለም መንግሥታት እና ማኅበረሰብ ድርጊቱን በጽኑ ከመቃወም እና ከማውገዝ በተጨማሪ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያፈላልግ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ጠይቋል፡፡

10 thoughts on “ሰበር ዜና – ቅ/ሲኖዶስ ከነገ ሚያዝያ ፲፬ ቀን ጀምሮ የሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ ዐወጀ፤ ቤተሰቦች የተሠው ክርስቲያኖችን ፎቶ፣ ስመ ክርስትና እና ሙሉ አድራሻ እንዲያቀርቡ አዘዘ – ‹‹ልጆቻችን የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን ናቸው››

  1. Tiruwork Abera April 21, 2015 at 12:00 pm Reply

    በቅድሚያ በልዑል እግዚአብሔር ስም ምስጋናዬን እያቀረብኩ፤ የመንግሥት ሰራተኛ ስለሆንኩ በምህላው ለመሳተፍ እንድችል ሰዓቱ ቢነገረን ጠዋት ከሥራ ሰዓት በፊት ወይም ከሥራ ሰዓት በኋላ ቢደረግ ከይቅርታ ጋር፤ ይህ የሁላችንም ጉዳይ ስለሆነ ብዬ ነው፡፡

  2. Anonymous April 21, 2015 at 1:03 pm Reply

    ሁሉ ነገር መልካም ሆኖ ሳለ ማነው ልጆቻችንን እየገደለና እያስገደለ ያለው ነውና ከመሰል ጥቃት ለመታደግ እንዲቻል ከመንግሥት ጋራ በቅርበት የሚሠራ ዐቢይ ኮሚቴ ይቋቋም የሚባለው ?

  3. Anonymous April 21, 2015 at 1:26 pm Reply

    Did I hear that the EOC has been trying to find out the identities of the martyrs? Hasn’t it found out who they were? If so, how could it make its announcement? Or why is it asking for their photos and God names? Shameful.

  4. Anonymous April 21, 2015 at 1:31 pm Reply

    የቤተክርስቲያን መሪዎች ከካድሬነት እራሳቸውን አርቀው ከምእመናን ጋር ቢሰሩ ለቤተክርስትያን:ለአባቶች እንዲሁም ለምእመናን መፈራትና መከበር ሞገስም ነበረ :: ከመንግስት/ወያኔ ጋር ያሽቃበጠ ኃጥያትን እንጂ ፅድቅን ሲሰራ አልተመለከትንም ለዚህም ማሳያው ገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማቃጠል ገዳማውያንና ምእመናንን ማሰቃየትና መገደል ነው :እነዚህ ሁሉ ሲፈፀሙ እንደ አቡነ ማትያስ ወፈፌውኤልያስ ሰረቀ …የተሃድሶ አበጋዞች … በማይመሰላቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ውስጥ ተቀምጠው ቤተክርስቶያንን እያደሙ በደስታ ሲፈነጩ ና ሲያላግጡ ተመልከተናል::ይህ ከመንግስት ጋር መስራት ከሰይጣን ጋራ ተባብሮ አዲስ ቤተክርስቲያንን የማጥቂያ ስልት መንደፊያ ነው:;ሲጀመር ወያኔ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ከኢትዮጵያ ምድር ሙሉ በሙሉ ማጥፋት በየካቲት ወር ፩፱፮፰ ባወጣው አላማ ላይ በግልፅ የተቀመጠ ጉዳይ ነው ::

  5. aberham April 21, 2015 at 1:59 pm Reply

    Adadis zena

  6. Anonymous April 21, 2015 at 2:27 pm Reply

    8ኛው ዘመነ – ሰማዕታት ???
    ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ነው፡፡ስለ ሃይማኖቱ በልቡ የሚያምነውን በአደባባይ በአፉ የሚመሰክር፡፡በምስክርነቱም፡- ግድያ/ግርፋት/መሰደድ/መታሰር የደረሰበት፡፡የሞት ቅጽበት ከመምጣቱ በፊት ያለው ሕይወት አይደለም ትልቁ የሰማዕትነት መመዘኛ፡፡በጭንቁ ሰዓት ሞትን ተጋፍጦ መመስከሩ ነው–እንደ ፈያታዊ ዘየማን የሞት ደጃፍ ላይ ቆሞ “ተዘከረኒ እግዚኦ በመንግስትከ–አቤቱ በመንግሥትሕ አስበኝ” ካለ ባይጠመቅ እንኳ ደሙ ጥምቀቱ ነው፡፡
    በኢ/ያ ከ20ኛ ክ/ዘ በፊት ባሉት አመታት፡- (1) በዮዲት ጉዲት፣(2)በሱስንዮስ፣(3)በግራኝ መሐመድ፣(4)በደርቡሽ ዘመናት በአማንያንና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የተፈጸሙ ድርጊቶችን የኢኦተቤክ “ዘመነ ሰማዕታት” ብላ መዝግባለች፡፡በ20ኛው ክ/ዘ እንዲሁ፡- (1)በጣሊያን ፋሺስቶች ወረራ በነአቡነ ጴጥሮስና በደብረ – ሊባኖስ መነኮሳት፣በምዕመናንና ካሕናት ላይ፣(2)በዘመነ – ደርግ በነፓትርያርክ ቴዎፍሎስና በተቀሩት ካሕናት ወምዕመናን፣(3)በዘመነ – ኢህአዴግ በ1984/5 ዓ.ም ጠባብ ብሔርተኞች ከጽንፈኞች ገጥመው በአሰቦትና ዐርባጉጉ ካሕናትና ምዕመናን ላይ፣በ1999 ዓ.ም በአርሲና(አንሻ) እና አጋሮ(ጅማ) በአክራሪዎች (ኻዋርጃ–የተሰኙ) የደረሰው እልቂት ሌላኛው ዘመነ – ሰማዕታት ተብሎ በእነ ነፍሰ-ኄር ሊቀካሕናት ክንፈገብርኤል አልታየ የተመዘገበ ነው፡፡አጠቃላይ በኢኦተቤክ ታሪክ ያለው ዘመነ – ሰማዕታት 7 ነው ሲሉ የቅድስት ቤ/ክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡6ትም የሚሉ አሉ፡፡
    የሊቢያው ከተፈጸመበት ቦታ፣ከፈጻሚዎቹ ዜግነት፣ከአፈጻጸሙ አሰቃቂነት አንጻር ራሱን ችሎ ዘመን ሊያስጠራ የሚችል ይመስለኛል፡፡አዎ!!እስካሁን በዐረብ ምድር ስላሉ ክርስቲያኖች ሰቆቃ በድርሳናቶቻችን አልዘገብንም፡፡እናም የሊቢያውን የኢ/ያ መስተጋድላን ተጋድሎ ተከትሎ በዜና – ሕይወታቸው ራስጌ “ዘመነ – ሰማዕታት ኢትዮጵያውያን በምድረ – ዐረብ ወአድያሚሃ” የሚል 8ኛ ዘመነ – ሰማዕታት ብንመዘግብላቸው ደገኛ ድርጊት ይኾናል፡፡
    አእርፍ እግዚኦ ነፍሰ – ኵሎሙ ክርስቶሳውያን እለ አእረፉ በርትዕት ሃይማኖት!!
    እንደ ስርዋጽ፡- ለኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወንድሞቻችን ምንም አንልም–ከመኩራት በቀር!!በየማኅበራዊ ሚዲያው ድርጊቱን ለመኰነን ከፊት ተሰለፉ!!እናም የተገመድንበት ውስጣዊ መንፈስ ስሪቱ ዘመናትንና ዘመነኛ አይዲዎሎጂ መሻገሩን አረጋገጡልን!!ምንም አንልም–ይሕን ልብ የሚነካ አብሮነት ክፉ አይይብን ከማለት በቀር!!እርግጥም የዚች ደሃ ሀገር የታላቅነት ምስጢር ቁሳዊ ሀብትና ንብረት ሳይሆን ሕዝቦቿ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለያቸው የፈተና ወራትን በተፋቅሮ የመወጣት ብልሃታቸው ነው!!ታዲያ እኮራለሁ!!ኀዘን ውስጥ ሆኜ እንኳ እኮራለሁ!!

  7. tesfaye.amenu April 21, 2015 at 3:49 pm Reply

    ዛሬም ነገም ወድፍትም አአይማኖቴ እምትላታለው

  8. Anonymous April 21, 2015 at 5:51 pm Reply

    ክቡራን የቅዱስ ሲኖዶስ አባቶቻችን የወሰዱት የአቋም መግለጫ እና ለሰማእታት ወገኖቻችን የተሰጠው ክብረ ሰማእታት ማዕረግ እጅጉን ስንጠብቀው የነበረ ስለሆነ እግዚአብሔር አህንም በእድሜና በማስተወል ከእግዚአብሔር ጋር ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆን ልዑል እግዚአብሔር የሚወደው ወዶትም የሚቀበለው የአገልግሎት ዘመን ይስጣችሁ ዘንድ የዘወትር ምኞታችን ነው ተጨማሪም የሰማዕታቱቤተሰቦችና ወገኖች በደረሰው አሰቃቂ ግፍ የተሞላበት ግድያ ምክንያት እያሳዩ ያሉት የሃዘንና የለቅሶ ልክ እንዲበጅለት
    ወደ ታላቅ ክብር መሸጋገራቸውን እንጂ በከንቱ እንዳልጠፉ ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ልታስተምር ይገባል ፣ ዞሮ ከሞት ውሎ ከቤት እንዲሉ የማይቀረውን ሞት እንዲህ በክብር በሰማዕታት ማእረግ ማረፋቸው ደስ ሊያሰኝ ይገባል እንጂ ሊያሳዝን አይገባም ትላንትና ግብጻዊያን ወንድሞቻችን የሰማዕትነት ክብር በተቀዳጁ ጊዜ እንዴት እንደተቀበሉት ቆም ብለን እስኪ እናስተውል

    በረከታቸው ይደርብን .

  9. Anonymous November 24, 2017 at 4:17 am Reply

    እ|ር ያፅናችሁ

Leave a comment